በኦሮሚያ የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ኮንሶርቲየም (CUCO) የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሓ ግብር በአርሲ ዩኒቨርሲቲ አካሂዷል፡፡ አረንጓዴ አሻራ የማኖሩ መርሓ ግብር የተካሄደው በዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ውስጥ የተዘጋጁትን ችግኞች በመትከል ነው፡፡ በዚህ መርሓ ግብር ላይ ክቡር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር፤ ክቡር አቶ ኡመር ሁሴን የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር፤ ፕ/ር ፍቃዱ በየነ የአየር ለውጥና የአካባቢ ጥበቃ ኮሚሽን ኮሚሽነር፤ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና የ14 ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶች እና ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
የዕለቱ መርሓ ግብር የተጀመረው በባህላዊው የኦሮሞ አባ ገዳዎች፡ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ምርቃት ሲሆን ዶ/ር ዱጉማ አዱኛ የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ነው፡፡ ዶ/ር ዱጉማ በዚህ ንግግራቸው እጽዋት የአየር ጠባይ ሚዛንን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው በመግለጽ የተተከሉትን ዛፎች የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እንክብካቤና ጥበቃ እንዲያደርግላቸው አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም ከአካባቢው ጋር ተስማሚ የሆኑትን አገር በቀል ችግኞች በመትከል በመጥፋት ላይ የሚገኙትን የእጽዋት አይነቶች ከመጥፋት መታደግ አለብን ብለዋል፡፡ በበኩላቸው ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር በስነ ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ምሁራን በምርምር የአረንጓዴ አሻራን ማገዝ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡