“በጎነት ለአብሮነት!” በሚል መርህ የብሔራዊ በጎ ፍቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ሥልጠና ጥር 5 ቀን 2013 ዓ.ም በአርሲ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሯል፡፡ “እንኳን በደህና መጣችሁ!” በማለት ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ልማትና ተማሪዎች ጉዳይ ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሜሮን ረጉ
በንግግራቸው ወጣቶች አገር ተረካቢዎች በመሆናችሁ በአገር ግንባታው በንቃት በመሳተፍ አገራችንን ከበለጸጉት አገሮች ተርታ ለማሰለፍ እና ሰላሟን ለማረጋገጥ በሚደረጉ ጥረቶች በንቃት በመሳተፍ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ ለመወጣት ራሳችሁን ዝግጁ ማድረግ ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡ በመቀጠልም ሰልጣኞቹ የመጡበትን ዓላማ ባለመዘንጋት የሚሰጠውን ሥልጠና በአግባቡ እንዲከታተሉ አሳስበው አርሲ ዩኒቨርሲቲ በሥልጠናው ላይ በሚቆዩባቸው ቀናት አቅም በፈቀደ መጠን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው እና ከጎናቸው እንደሚቆም ገልጸዋል፡፡
የኢፌዲሪ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ለሁሉም የሥልጠናው ተሳታፊዎች ከማእከል በቬርቹዋል ባስተላለፉት መልዕክት ሥልጠናው በተለያዩ ርእሶች ላይ እንደሚሰጥ በመግለጽ እንደዚህ አይነቱ ለወጣቶች የሚሰጠው ሥልጠና ወጣቶች በአገር ግንባታው ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡ የመጀመሪያው ዙር የብሔራዊ በጎ ፍቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ሥልጠና ለ45 ቀናት በተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጥ ሲሆን ሰልጣኞቹ ከሁሉም የአገራችን አካባቢዎች የመጡ ናቸው፡፡